የቤተ ክርስቲያን መረጃ መፈለጊያ

ሐዋርያዊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያልደረሰችበት የዓለም ክፍል የለም ማለት ይቻላል። በተለይ በአርቆ አስተዋይ የወቅቱ የቤተክርስቲያን መሪዎች መልካም ፈቃድ ወደ ምእራቡ ክፍለ ዓለም ጉዞዋን ከጀመረችበት ከ 1960 ዓ/ም ጀምሮ ቤተ ክርስቲያኗ በልዪ ልዪ ምክንያት ሀገር ወገናቸውን ለቀው ከተሰደዱ ኢትዮጵያውያን አልፋ አነሰም በዛ ለባዕዳኑ ሕዝብም የክርስትና ሕይወት ልምላሜ እየሆነች ትገኛለች። የቤተክርስቲያኗ ዲያስጶራዊ እንቅስቃሴ በተጠናና አንድነት በተመላበት መልኩ ቢመራ፣ ብዙ ጊዜ እንደሚባለው ክርስትና እየጠወለገች በሄደችበት የምዕራቡ ዓለም ታላቅ ተስፋ /Hope of Christianity in the world/ መሆን እንደምትችል ጥርጥሬ አይኖርም። ቤተ ክርስቲያንን በደሙ የመሠረተ አምላክ የራቀውን እንዲያቀርብ፣ የተጣመመውን እንዲያቀና፣ አባጣ ጎርባጣውን እንዲያስተካክል ሁላችንም ልንጸልይ ያስፈልጋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሙሉ ፈቃድ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥር ታቅፎ አገልግሎቱን ሲሰጥ ሁለት ዐሠርት ዓመታትን ያስቆጠረው ማኅበረ ቅዱሳን አሁንም በእግዚአብሔር ፈቃድ፣ በአበው ቡራኬና መመሪያ እንዲሁም በምእመናን ጸሎትና ዕርዳታ አገልግሎቱን ይቀጥላል። የተመሠረተበት ዋና ዓላማ ጥንታዊት፣ ታሪካዊትና ዓለም ዐቀፋዊት ቤተ ክርስቲያናችን ከመንበር ሀገሯ አልፋ በዓለም እንድትታወቅ፥ ትምህርተ ሃይማኖቷ፣ ሥርዓተ እምነቷና ትውፊቷ ተጠብቆ ለሰው ዘር በሙሉ እንዲሰበክ ማድረግ ነው። ማኅበሩ በቤተ ክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ ተወስኖና ተለክቶ የተሰጠውን ይህንን ዓላማ ከግብ ለማድረስም ልዩ ልዩ የአገልግሎት መስመሮችን ዘርግቶ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፣ ወደፊትም ይቀጥላል።

ይህ የመረጃ ቋት /the database/ በሀገር ውስጥም ይሁን በውጭው ዓለም ቤተ ክርስቲያን ነክ የሆኑ መረጃዎችን ለምእመናንና ቤተ ክርስቲያኗን ለሚፈልጓት ሁሉ ማድረስን ዐቢይ ዓላማው አድርጎ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ማኅበረ ቅዱሳን ሚዲያ ዋና ክፍል ተዘጋጅቷል። ይህ ዝግጅት ቤተክርስቲያናችንን አስመልክቶ በዓይነቱም ይሁን በይዘቱ የመጀመሪያ እንደመሆኑ መጠን በሒደት እየዳበረ የሚሄድና የሁሉንም የቤተ ክርስቲያን አካላት ሱታፌ የሚጠይቅ ነው። በመሆኑም የመረጃ ቋቱ ተጠቃሚዎች ይጠቅማል የምትሏቸውን መረጃዎችን በመላክ ሱታፌ እንድታደርጉ የመረጃ ቋቱ ዝግጅት ክፍል በዚሁ አጋጣሚ ጥሪውን ያስተላልፋል። መረጃዎችን በዚህ ገጽ፣ አስተያየትዎን ደግሞ በዚህ ገጽ፣ እንዲልኩልን በእግዚአብሔር ስም እናሳስባለን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ማኅበረ ቅዱሳን ሚዲያ ዋና ክፍል

ወደ ዋናው ገጽ ይመለሱ